08 MARCH 2015 ተጻፈ በ 

-በምርጫ ክልል 17 (ቦሌ) ከፍተኛ ትንቅንቅ ይጠበቃል

ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ለመወዳደር፣ በአዲስ አበባ 23 የምርጫ ክልሎች የኢሕአዴግ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የተቃዋሚ ፓርቲዎች ተወካዮች ተለይተው ታወቁ፡፡

በዘንድሮው ምርጫ በአዲስ አበባ ኢሕአዴግን ወክለው አንድ ሚኒስትርና አራት ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ እንዲሁም የቢሮ ኃላፊዎች ይወዳደራሉ፡፡ በዚህም መሠረት ኢሕአዴግን ከሚወክሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የመልካም አስተዳደር የሲቪል ሰርቪስ ክላስተር አስተባባሪና የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር ወ/ሮ አስቴር ማሞ፣ የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተመስገን  ጥላሁን፣ የንግድ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዓሊ ሲራጅ፣ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታደሰ ኃይሌ ፓርቲውን ይወክላሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የአዲስ አበባ ከተማ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ፍሬሕይወት አያሌውና የአማራ ልማት ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ብሥራት ጋሻውጠና፣ በአዲስ አበባ ኢሕአዴግን ወክለው የሚወዳደሩ ዕጩዎች ናቸው፡፡

ሃያ ሦስት የምርጫ ክልሎች ካሉት የአዲስ አበባ ከተማ የምርጫ ክልሎች ሁሉ በተለየ ሁኔታ በምርጫ ክልል 17 ወይም በቦሌ አካባቢ ከፍተኛ የሆነ ፉክክር፣ በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የምርጫ ክልሉን ልዩ የሚያደርገው ደግሞ የሚወዳደሩት ዕጩ ተወዳዳሪዎች በየፓርቲያቸው ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የሥራ ድርሻ ይዘው የሚገኙ መሆናቸው ነው፡፡ በዚህም መሠረት በዚህ የምርጫ ክልል ኢሕአዴግን ወክለው የሚወዳደሩት የቀድሞው የክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስፈጻሚና የአሁኑ የአዲስ አበባ የኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዮሐንስ በቀለ ናቸው፡፡

በዚሁ የምርጫ ክልል የሰማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ፣ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ወንድወሰን ተሰማ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮ ከገዥው ፓርቲ ጋር የሚፎካከሩ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች ናቸው፡፡

ከዚህ የምርጫ ክልል በተጨማሪ ጳውሎስ ሆስፒታል አካባቢ የሚገኘው የምርጫ ክልል ስምንትም፣ እንዲሁ በተቃዋሚ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች መካከል የሚካሄድ ከፍተኛ ፉክክር ይጠበቃል፡፡ በዚህ የምርጫ ክልል የሰማያዊ ፓርቲ ፋይናንስ ኃላፊ አቶ ወረታው ዋሴና የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) ፕሬዚዳንት አቶ ትዕግሥቱ አወሉ ከሌሎች ተወዳዳሪዎች ጋር የሚያደርጉት ፉክክር ይጠበቃል፡፡

ሁለት የተቃዋሚ ፓርቲ ፕሬዚዳንቶችን የሚያገናኘው የምርጫ ክልል ደግሞ ሰሜን ማዘጋጃ አካባቢ የሚገኘው የምርጫ ክልል አሥር ሲሆን፣ በዚህ የምርጫ ክልል የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ (ቅንጅት) ፕሬዚዳንት አቶ አየለ ጫሚሶና የአዲስ ትውልድ ፓርቲ (አትፓ) ፕሬዚዳንት አቶ አስፋው ጌታቸው ይፋጠጣሉ፡፡ በዚህ የምርጫ ክልል የኢሕአዴግ ተወካይ የሆኑት የአዲስ አበባ ኮንስትራክሽንና ቤቶች ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ኃይለ ማርያም ይወዳደራሉ፡፡

ሌላኛው የተቃዋሚ ፓርቲ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፕሬዚዳንት ደግሞ አቶ አበባው መሐሪ፣ ጦር ኃይሎች አካባቢ በሚገኘው የምርጫ ክልል 24 ተወዳዳሪ ናቸው፡፡ የአዲስ አበባ ቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ አሊማ ባድገባ ኢሳ ኢሕአዴግን ወክለው ይወዳደራሉ፡፡

ዘንድሮ በከተማው ከሚወዳደሩት የኢሕአዴግ ዕጩ ተወዳዳሪዎች መካከል 15 ያህሉ አዲስ ተወዳዳሪዎች ሲሆኑ፣ ሰባቱ ደግሞ ነባር ተወዳዳሪዎች ናቸው፡፡ አንድ ተወዳዳሪ ደግሞ አዲስም ይሁኑ ነባር የተገለጸ ነገር የለም፡፡

ባለፈው አጠቃላይ ምርጫ ፓርቲውን ወክለው ተወዳድረውና አሸንፈው የነበሩት የገንዘብና የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር አብርሃም ተከስተ፣ የውኃ፣ የመስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር አቶ ዓለማየሁ ተገኑ፣ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር ወ/ሮ በላይነሽ ተክላይ፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሽመልስ ከማል፣ እንዲሁም የንግድ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ያዕቆብ ያላ ዘንድሮ በከተማው አይወዳደሩም፡፡ አቶ ዓሊ ሲራጅ፣ አቶ ዮሐንስ በቀለ፣ ወ/ሮ ዳግማዊት ምስጋናና አቶ ታደሰ ኃይሌ ደግሞ በከተማው የሚወዳደሩ አዳዲስ ዕጩዎች ናቸው፡፡

Leave a Reply